Friday, November 6, 2015

"አውሮፓን ጅብ ያስበላ የሉተር ስብከት በተዋሕዶ መድረክ"(ክፍል ሁለት)

፨ የሉተር ልጆች ፍጻሜ :-የግብረ ሰዶማውያንን ጋብቻ በ”ኢየሱስ”ስም መባረክ

፨ ዓለማችን ጆሮን የሚበጥስ የግብረ ሰዶማውያንን ዜና መስማት ከጀመረች ሰነበተች፡፡አሁን አሁን አንዳንድ በሥልጣኔ ላይ ያሉ ሀገሮች በገሃድ ለግብረ ሰዶማውያን ፈቃድ መስጠት ጀምረዋል፡፡ያለንባት ሰሜን አሜሪካም ይህንን የጥፋት ተግባር የመጨረሻ ውሳኔ በሚሰጠው ፍርድ ቤቷ አጽድቃ እግዚአብሔርን በአደባባይ አሳዝናለች፡፡ቀደም ባለው ዘመን አበው በትርጓሜያቸው የ666 መነሻ አንዱ ምልክት ይህ ጥፋት እንደሆነ ጽፈው ነበር፡፡በዚያን ጊዜ በመጨረሻው ዘመን ይህ ይሆናል ብሎ ለማመን ብዙ ሰው ተቸግሯል፡፡አሁን ግን ዓለማችን ወደ ፍፃሜ እያመራች መሆኑን ግልጽ በሚያደርግ መልኩ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ በሕግ ሲጸድቅ እያየን ነው፡፡ለዛሬ ይህን ርእስ ያነሳነው መንግስታት በግብረ ሰዶማውያን ላይ ስላላቸው አቋም ለመነጋገር አይደለም፡፡ይህ በየዕለቱ በዜና ማሰራጫ የምንሰማው ስለሆነ አዲስ አይሆንብንም፡፡የሚገርመው ግን የግብረ ሰዶማውያንን ጋብቻ በአዋጅ የተቀበሉ የእምነት ድርጅቶች መኖራቸው ነው፡፡ባለንበት ዘመን ወንጌል ገልጠው እያስተማሩ የክርስቶስ ደቀመዛሙረት ነን እያሉ ግብረ ሰዶማውያንን በመቅደሳቸው አቁመው የሚድሩ የእምነት ድርጅቶች ስለመኖራቸው ቢያነቡ ምን ይሰማዎታል ? ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ እንዲሉ እንዲህ ያለው የጥፋት ተግባር በ”ኢየሱስ”ስም ጸሎት እየተደረገ የሚባረከው በሉተር ልጆች አዳራሽ በፕሮቴስታንቶቹ "አብያተ ክርስቲያናት" ነው፡፡

Sunday, October 18, 2015

አውሮፓን ጅብ ያስበላ የሉተር ስብከት በተዋሕዶ መድረክ (ክፍል አንድ)

ከሀገር ቤት ከወጣሁ አሥረኛ ዓመቴን እየያዝኩ ነው፡፡በዚያን ጊዜ የፕሮቴስታንት ተሐድሶ መናፍቃን በቡድን በመደራጀት እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡እኛ ያልዘመርንበት ሰርግ ምኑን ሰርግ ሆነ፡፡እኛ ያልተገኘንበት ጉባኤ እንዴት ጉባኤ ሊባል ይችላል በሚል የሌላውን አገልግሎት ሁሉ ባዶ አድርገው እራሳቸውን ሲያስቀድሙ አስታውሳለሁ፡፡በወቅቱ ከጥቅም አንጻር ብቻ የሚደራጁ የመሰላቸው ጥቂቶች አልነበሩም፡፡አካሄዱ ግን ከጥቅም ባለፈ ሌላ የተለየ ዓላማ ከጀርባው እንደነበረበት ያስታውቃል፡፡ያን ጊዜ በተደጋጋሚ ሲናገሩት የሚሰማ ትልቁ አጀንዳቸው “ጌታ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አልተሰበከምና እርሱን መግለጥ አለብን” የሚል ነው፡፡ይሄ አጀንዳ ደግሞ ምንጩ ማን እንደሆነ እናውቀዋለን፡፡እነዚህ ቀሚሳችንን ለብሰው በድፍረት የሚውረገረጉ ውሉደ መርገም የተሐድሶ ማናፍቃን ተላላኪዎች ናቸው፡፡እንዲህ የሚሯሯጡት የተሰጣቸውን ተናግረው የእለት ጉርስ ለማግኘት ነው፡፡ዋነኞቹ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ይህ መልእክት እንዲተላለፍ የሚፈልጉት ግን በምዕራቡ ዓለም የዘሩት የሉተር እምነት የጠወለገባቸው ፕሮቴስታንቶቹ ናቸው፡፡ፕሮቴስታንቶቹ የሉተር እምነት በምድር አውሮፓ ጠውልጎና ደርቆ ሲመለከቱ ለጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን “ጌታን ሊገልጡ” ሚሴዎናውያንን ላኩ ሚሴዎናያኑ ደግሞ የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆችን ልከው ሕዝቡን ማደናቆር ያዙ፡፡ለቀባሪ ማርዳት ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

በአውሮፓ ተዘርቶ ያልበቀለ፣ሕዝቡን ለእስልምና እና እግዚአብሔር የለም ለሚል ፍልስፍና አሳልፎ የሰጠ ከንቱ እምነት፣ሉተር የመሠረተው የፕሮቴስታንት እምነት እኛ ሃገር ለመዝራት መሞከር ተሳልቆ ወይም ምቀኝነት እንጂ ሌላ ምን ይሉታል፡፡በምድረ አውሮፓ ወደ ሉተራውያን"ቤተ ክርስቲያን"የሚሄድ ሕዝብ ጠፍቷል፡፡ከዚህ ይልቅ ሕዝቡ እግዚአብሔር የለም በሚል ፍልስፍና ኢአማኒ ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡በሚሺነሪ ታሪክ የምትታወቀው አፍሪካን በፕሮቴስታን እምነት ለማጥለቅለቅ ሌተ ተቀን የምትሰራው ስዊድን እንኳን ከሕዝቧ ቁጥር 34 ፐርሰንቱ እግዚአብሔር የለም ብሎ እንደሚያምን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡የእግዚአብሔር መኖር የሚያምነው ደግሞ 27 ፐርሰንት የሚሆነው ብቻ ነው፡፡በፈረንሳይም 40 ፐርሰንት የሚሆን ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕልውና የማይቀበል ሰሆን የእግዚአብሐር መኖር አምኖ የሚቀበለው ደግሞ 18 ፐርሰንት ብቻ ነው፡፡በመካከል የለም አለ ሳይል የሚኖር ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ እንዳለም ልብ ይበሉ(1)፡፡

Wednesday, July 22, 2015

አገልግሎት

              (ክፍል አንድ)
አገልግሎት ለእግዚአብሔር ያለንን ጽኑ ፍቅር የምንገልጥበት መንገድ ነው፡፡በሰማይ በዙፋኑ ፊት ያሉ እልፍ አእላፋት መላእክት ለሰው ልጆች ቤዛ ሆኖ በፈቃዱ ለተሰቀለልን አማናዊ  በግ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሰግዳሉ(ራእ ዮሐ -)፡፡እርሱን ሌትና ቀን ያመሰግናሉ፡፡ይህም ስለሰው ልጆች ሲል የሠራውን በማሰብ መሰቀሉን፣መሞቱን፣መነሣቱን በማሰብ የሚፈጸም የፍቅር አገልግሎት ነው፡፡ይህን በሰማይ የሚፈጸም መንፈሳዊ አገልግሎት በምድር ላይ መድገም፣ኃጢአት በበዛበት ዓለም ላይ ሆኖ ፈጣሪን ለማስደሰት መዘጋጀት መመረጥ ነው፡፡

ወዳጄ እግዚአብሔር እንድታገለግለው መርጦሃል፡፡እርሱ በሰጠህ ጤና፣አካል፣ገንዘብ፣መልሰህ እርሱኑ ታገለግል ዘንድ ጸጋውን ሰጥቶሃል፡፡ከሁሉ አስቀድሞ ለዚህ ታላቅ ሥራ ስለመረጠህ ፈጣሪህን አመስግን፡፡አስተውል በዓለም ላይ የሰው ልጆች የሚሠሩት ታላላቅ ሥራ ሁሉ ተደምሮ ፈጣሪን ማገልገልን ሊመስል ሊያክል አይችልም፡፡ሌላው ሥራ ሁሉ በዚህ ዓለም የሚቀር ነው፡፡ዋጋውም በምድር ላይ መደሰት፣መደነቅ፣መከበር ሊሆን ይችላል፡፡መንፈሳዊ አገልግሎት ግን በምድር በረከትን በሰማይ ገነት መንግሥተ ሰማያትን ያሰጣል፡፡

Wednesday, July 15, 2015

ክርስትናና ወጣትነት ( ክፍል ፲፩)

           
                                                                                                              (ካለፈው የቀጠለ፡-ቅናት መንፈሳዊ)
በመናፍቃን መነሣት መቅናት
ሰይጣን፡-ቤተ ክርስቲያንን ለመፈታተን፥የሰው ልጆችን ዋሻ ማደሪያ አድርጎ ያስነሣል፡፡የግብር ልጆቹ  መናፍቅ ሆነው ሌላውንም መናፍቅ ለማድረግ እንዲነሣሡ ይገፋፋል፡፡መናፍቅ ማለት ተጠራጣሪ ማለት ነው፡፡ሀልዎተ እግዚአብሔርን ፣የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት፣የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና የአማላጅነት ሥልጣን፣የቅዱሳንን አማላጅነት…ተጠራጥረው ትውልዱንም የሚያጠራጥሩ ሐሰተኛ መምህራንን ያስነሣል፡፡በዚህም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ  ደም የተመሠረተች፣በቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት በዓለም የተስፋፋች ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማወክ ሌትና ቀን ሥራ ይሠራል፡፡አንዳንዴም ምእመናንን ግራ ለማጋባት መናፍቃንን ከሩቅ ብቻ ሳይሆን ከቅርብም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኙ አገልጋዮች መካከል ያስነሣል፡፡ይህም፡- አስቀድሞ በሐዋርያት የተነገረ እውነታ ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎስ፡- ሰይጣን መናፍቃንን ከቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልጋዮች መካከልም ሊያስነሣ እንደሚችል “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ”ብሏል።የሐዋ፡፳፥፳፰፡፡በዘመናችን ቀሚስ ለብሰው በየዓውደ ምሕረቱ የሚታዩ ፥በሥራ እና በተግባር ግን ለሌላው የእምነት ድርጅት ጠበቃ የሚሆኑ መናፍቃንን የምንመለከተውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡

ጠላት ከጌታ ጉባዔ፡- ይሁዳን፥በዘመነ ሊቃውንት፡-አርዮስን፥መቅዶንዮስን፥ንስጥሮስን እንዳስነሣ ሁሉ፥ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን እንዲፈትኑ፥ ፀረ ተዋሕዶ፥ፀረ ማርያም የሆኑ የ”ተሐድሶ”አራማጆችን ይልካል፡፡እንዲህ ባለው ክፉ ዘመን፥ የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ከምናይ መከራውን ታግሰን ለመቀበል መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡እግዚአብሔር ቤቱን መጠበቅ አያቅተውም፡፡እርሱ ከፈቀደ መናፍቃንን በአንድ ቀን ጠራርጎ ማስወገድ ይችላል፡፡ሁሉን በዝምታ የሚያልፈው፥ አንድም ስለትዕግስቱ ብዛት፥በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ለሃይማኖት ያለን ቅናት ይመዘን ዘንድ ነው፡፡እንደ ቅዱስ ዳዊት፡“እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤የቤትህ ቅንዐት በልታኛለችና፤”መዝ፡፷፰፥፱።ብለን መነሣት አለመነሣታችንን ለመመልከት ነው፡፡እርሱ ያውቀዋል፥ነገር ግን ለእኛ ድካማችንን ፊት ለፊት ሊያሳየን ነው።መናፍቃን፡-ቤተ ክርስቲያንን ሲወጉ፥በተአምረ ማርያምና በገድላተ ቅዱሳን ሲቀልዱ፥በታቦቱና በቅዳሴው ሲሳለቁ፥ አይተን እንዳላየን ብንሆን፥በባልንጀርነት ሰበብ መምከር ወይም መለየት አቅቶን በዝምታ ብናሳልፍ፥ለመሸፋፈንም ብንሞክር፥በምእመናን ነፍስ መጥፋት ተጠያቂ እንሆናለን፡፡በተዋሕዶ አምላክ የእውነት ሚዛንም ተመዝነን ቀለን እንገኛለን፡፡

Wednesday, July 8, 2015

                                                              ”ቤተ  ደጀኔ”
መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው በሚሰብከው ስብከት በሚጽፈው መንፈሳዊ መልእክት ለብዙዎች መጽናናትና ወደ እግዚአብሔር መመለስ ምክንያት ሆኗል፡፡እጅግ አድርገን የምንወደውና የምናከብረው ታናናሽ ወንድሞቹ ሁልጊዜም በአርያነት የምንጠቅሰው የቤተ ክርስቲያንችን ዕንቁ አገልጋይ ነው፡፡በቃሉ ብቻ ሳይሆን በሕይወቱም ጭምር ስለሚያስተምር የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ሁሉ ለእርሱ የተለየ አክብሮት አለን ፡፡የመልአከ ሰላም ብሎግ “ቤተ ደጀኔ” ብዙዎችን ሲያስተምር ቆይቶ በመካከል በመቋረጡ መልሶ ሥራ የሚጀምርበትን ጊዜ በናፍቆት ስንጠባበቅ ቆይተናል፡፡እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ በዚህ ሳምንት “ቤተ ደጀኔ” የነበረበትን የቴክኒክ ችግር አስተካክሎ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡በዚህም የ”ቤተ ደጀኔ”ብሎግ አንባቢዎች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡ቤተ ደጀኔ betedejene.org በሚለው የቀድሞ አድራሻ ሳይሆን በአዲሱ አድራሻው http://www.betedejene.com ብላችሁ ታገኙታላቸሁ፡፡መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራውን በሕይወት በጤና ይጠብቅልን፡፡ረጅም የአገልግሎት ዕድሜ ያድልልን እላለሁ፡፡መልካም ንባብ፡፡

Wednesday, July 1, 2015

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የአንድነት ጉባኤ              

 ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ነው እኔ ካለሁባት ከኮለምበስ ኦሀዮ ሁለት ሰዓት ነድተን ክሊቭላንድ ለመድረስ በጠዋት ጉዞ ጀምረናል፡፡ክሊቭላንድ  ላይ አንድ የተለየ መርሐ ግብር  አለ፡፡ሰሞኑን በወንድሞቻችን ላይ የደረሰው መከራ ውስጣችንን  አናውጦት የከረመ ቢሆንም የዛሬው ፕሮግራም ግን እጅግ መጽናኛ ሊሆነን እንደሚችል እያሰብን እንገሰግሳለን፡፡ከፊት ለፊቴ  በሌላ መኪና ከኤርትራ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዲያቆን መድኀኔ እና ኃየሎም እየተዙ ነው፡፡ከጠዋቱ   8፡30 am ክሊቭላንድ ደረስን፡፡በቀጥታ መርሐ ግብሩ ወደሚከናወንበት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አመራን፡፡በቅዱስ ማርቆስ ስም የተሰየመው ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ቦታ ይዞ በርቀት ሲታይ የተለየ ግርማ አለው፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሰሜን አሜሪካ ሲመጡ የሚያርፉበት እና ትልቁ ካቴድራላቸው መሆኑን እሰማ ነበር ዛሬ በዓይኔ  ተመለከትኩት፡፡መኪናችንን በውጭ አቁመን ወደ ትልቁ ከቴድራል ገባን፡፡

የተወሰኑ ትናንሽ አዳራሾችን አለፍንና ወደ ዋናው ቤተ ክርስቲያን ደረስን፡፡ሕዝቡ ግጥም ብሎ ሞልቶታል፡፡የቅዳሴው ሥርዓት የሚጀምረው 9 am ሰዓት ላይ ስለሆነ ምእመናን ለማስቀደስ ይጠባበቃሉ፡፡እነዚህ ምእመናን ለየት የሚደርጋቸው ከተለያየ ሀገር የተሰበሰቡ መሆናቸው ነው፡፡ከህንድ፣ከግብጽ፣ከአርመን፣ከሶሪያ፣ከኢትዮጵያ፣ከኤርትራ የታደሙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ናቸው፡፡ምእመናኑን አልፈን ወደ  ቤተ መቅደስ ስንቃረብ የጉባኤው አስተባባሪ ግብጻዊ ዲያቆን ወደ እኛ ሲመጣ አየነው፡፡ቀረበና ወደ ውስጥ ወደ መቅደስ እንድንገባ ጋበዘን፡፡ተያይዘን ገባን፡፡በቤተ መቅደስ ካህናት ግጥም ብለው ሞልተዋል፡፡ከእህት አብያተ ክርስቲያናት የተሰበሰቡ የተለያየ የሚናገሩ መልክና ቀለማቸውም የተለያዩ ነበሩ፡፡በታቦቱ ፊት ግን አንድ ሆነው  ተሰልፈዋል፡፡የህንድ፣የግብጽ፣የአርመን፣የሶሪያ ፣የኢትዮጵያ እንዲሁም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ናቸው፡፡ቅዳሴው ግብጻውያን እየመሩ ሁሉም በአንድ ላይ እያገለገሉ መከናወኑን ቀጠለ፡፡

Wednesday, April 29, 2015

“እስመ በእንቲአሁ ይቀትሉነ ኲሎ አሚረ ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ”
“ስለእርሱ ሁል ጊዜ ይገድሉናልና እንደሚታረዱ በጎችም ሆንን፡፡ ”(መዝ 43-22)ለመሆኑ ጠላት ዲያብሎስ በእነዚህ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ላይ የጥፋት ዘመቻውን የከፈተው ለምን ይመስልዎታል? እስካሁን እንዳየነው ጠላት ዲያብሎስ አሸባሪዎቹን ለጥፋት አስነስቶ የሶሪያን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡የግብጽን ልጆች በአደባባይ ሰውቷል፡፡አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ የጥፋት ሰይፉን ሲመዝ አይተናል፡፡የኤርትራም ቤተ ክርስቲያን የዚህ ዘመቻ ተጠቂ ናት፡፡

እነዚህ አብያተ ክረስቲያናት በጠላት ጥርስ ውስጥ የገቡበት ከዓለሙ ተለይተው በእስልምና አክራሪዎች የሽብር ተግባር ፊተኛ ተጠቂ የሆኑበት... ምክንያት ምን ይሆን ?የተዋህዶን ክብር የሰው ልጅ ባይረዳውም ፣ዓለሙ ጠንቅቆ ባያውቀውም፡፡ሰይጣን ግን ያውቀዋል፡፡ ስለዚህ ዛቻውን ሰይፉን በተዋሕዶ ልጆች ላይ አደረገ፡፡ተዋሕዶ ለሰይጣን የግብር ልጆች ዋነኛ ጠላት ሆነች፡፡ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ያላትን ክብርና መወደድ በግልጥ የሚያስረዳ ነው፡፡ለነገሩ ሌባ ንብረት ካለበት እንጂ በሌለበት ምን ይሰራል፡፡ባንቺ ያለውን ጸጋና በረከት ስለሚያውቀው ዛቻውን ሰይፉን በልጆችሽ ላይ መዘዘ፡፡ይህም ሆኖ ግን ጥይቱን ይጨርሳል እንጂ እስከ እለተ ምጽአት ወልድ ዋሕድ እያልሽ መመስከርሽን ማስቀረት አይቻለውም፡፡

                                                                      ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል